Menu

Alem Cinema

Connect with us

ተዋናይት ሀና መርሃፅድቅ

Posted on Dec 13, 2019

ከአስር ፊልም በጣም የሚገርመኝ መነሻ ታሪኩ ነው!

ተዋናይት ሀና መርሃፅድቅ

ልክ እንደጮራ በምስራቅ በኩል የተከሰተች ወጣት የጥበብ ፈለግ ተከታይ ናት። የበረሃ ሰዎች መኖሪያ፤ የአርብቶ አደሮች መዘዋወሪያ፤ የግመሎችና ፍየሎች መናሀሪያ በሆነችው በተለይ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚበዙባት ሱማሌ ክልል ውስጥ እሷ በኦርቶዶክስ ቤክርስቲያን አፀድ በቀሳውስት አባቶች ስር ተማሪነትን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጋር አስማመምታ ነው ያደገችው። ተወልዳ ያደገችው ጅጅጋ ከተማ ነው። ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን እናቷ እሷን ሲወልዱ ገና በልጅነት እድሜ ላይ እንደነበሩ ትናገራለች። በዚህ ምክንያት ለእናቴ ልዩ ቦታ አለኝ የምትለው እንግዳችን አባቷም የቤተ ክህነት ሰው መሆናቸው በአስተዳደጓ ላይ የራሱን በጎ አስተዋፅኦ አድርጓል ብላ ታምናለች። በቴሌቪዥን ከምታያቸው ሰዎች መካከል በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምርት ቤት ኀላፊ የነበሩትን ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየን እና የማለዳ ኮከቦች የትወና ውድድርን በዳኝነት የሚመሩት ባለሙያዎች አንድ ቀን ትወና እንደሚያስተምሯት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በውስጧ የእርግጠኝነት ስሜት ነው የነበራት። ቴአትር የመማር ከፍተኛ ፍላጎትም ያሳደረችው እዛው ጅጅጋ በነበረችበት ወቅት ነው። ይህን ህልሟን ለእናቷ ትነግራቸው እንደነበርም ትናራለች። ይሁንና የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ አጠናቅቃ ዩኒቨርሲቲ ስትመደብ ያልተጠበቀ ነገር ተፈጠረ። ከፍላጎቷ ውጭ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሶሻል ሳይኮሎጂ እንድትማር ተመደበች። እናም ከእርሷ አልፎ ቤተሰቡ በእጅጉ አዘነ። በተለይ ወላጆቿ የልጃቸው የረጅም ጊዜ ህልምና ምኞት ባለመሳካቱ ከእሷ በላይ አስጨንቋቸዋል። በ2007 ዓ.ም ከበረሃማው የጅጅጋ አየር ወደ ቆፈናሟ ደብረብሃን ተጓዘች። ነገር ግን ከአካላዊው ቅዝቃዜ የላቀ ፍላጎትን የማጣት ብርድ በልብስ የማይከላከሉት በመሆኑ የውስጥ ስሜቷን በረደው። ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ህይወት ተጀመረ። ነገር ግን የልቧን መሻት ወደማይሞላ ስፍራ ልጃቸውን የሸኙት ወላጆቿ ተስፋ ቆርጠው ከመቀመጥ ይልቅ ልጃቸው የምትፈልገውን የማግኘት እድል ይኖራት እንደሆነ ማጠያየቅ ጀመሩ። የቴአትር ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰጥ እርግጠኞች ናቸው። ግን ያን እድል እንዴት ማግኘት ይቻላል የሚለውን አያውቁም። አባቷ ስራዬ ብለው ጉዳዩን የሚውቁትን ሁሉ አስጠይቀውና አጣተርተው ተስፋ ያለው ፍንጭ አገኙ። ዩኒቨርሲቲው በቀጥታ ከሚቀበላቸው መደበኛ ተማሪዎች በተጨማሪ ፍላጎቱ ኖሯቸው እድሉን ላጡ እንደሷ አይነት ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና እየፈተነ ያለፉትን እንደሚያስተናግድ ሰሙ። እናም ተነገራት። ምንም እንኳን በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መማር የጀመረች ቢሆንም እድሉን ሳትሞክር መተው አልፈለገችምና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፈተናውን ወሰደች። አለፈችም። የህይወቷን አቅጣጫ የቀየረችበትም ሆነ። በቃ ከአንድ ወር የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ ተስፋ የቆረጠችበት የቴአትር ትምህርቷን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጠለች። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ገና ከአንደኛ አመት የተማሪነት ጊዜ ጀምሮ ሙያው ላይ የመሳተፍ እድሎችም ተፈጠሩላት። በርካታ ስራዎችን እስከተመረቀችበት ጊዜ ድረስ ለመስራት ችላለች። ከተመረቀችበት ማግስት ጀምሮም አላረፈችም። በቴአትር ብትመረቅም ፍላጎቷ ፊልሙ ላይ ያመዝን ነበርና ፊልሞችን መስራት ቀጠለች። ማስታወቂያዎች፣ የሙዚቃ ቪዲዮ ትወናዎች፣ የቴሌቪዥን ድራማ ላይም አልቦዘነችም። አሁን አሁን ከትወናው በዘለለ የዳይሬክቲንግና የድርሰት ስራው ላይም እየሰራች ትገኛለች። በቅርቡ ደግሞ አስር የተባለ አዲስ ፊልም ላይ መስራቷን ምክንያት በማድረግ ለእንግድነት መርጠናታል። በዚህ አጋጣሚ እስካሁን የሰራችባቸው ፊልሞች ብዛትም አስር ይደርሳሉ። ነገር ግን ይህ ከፊልሙ ጋር የሚገናኝ አይደለም። ጊዜው በፈቀደልን ልክ ስለሁሉም አውርተናታል። የዛሬዋ የዓለም ሲኒማ እንግዳችን ወጣቷ ተዋናይት ሀና መርሃፅድቅ ናት። አብራችሁን ቆዩ።

አለም ሲኒማ፡- ሀኒ በቅድሚያ ለጊዜሽ አመሰግናለሁ። እስቲ ከቀላል እንጀምር የአባትሽን ስም የሚያሳስቱ ሰዎች ገጥመውሽ አያውቁም? መርሃፅድቅ ያለተለመደ ዓይነት ስም ነው።

ሀና፡- ልክ ነህ ብዙ ሰው ያሳስተዋል። እኔ ደሞ ሲያሳስቱት በጣም ነው የሚያናደኝ። መርሃፅድቅ ማለት የፅድቅ መሪ ማለት ነው። እንዳልከው ብዙ ያልተለመደ ስም ስለሆነ ሰዎች ያሳስቱታል።

አለም ሲኒማ፡- ስለልጅነት ጊዜሽ እናውራ ምን ትዝ ይልሻል?

ሀና፡- ልጅ ሆኜ የተማርኩት በኦርቶዶክስ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ስለዚህ የቄስ ትምህርትም አብረን እንማር ነበር። ከትምህርት ቤት ስንፎርፍ እንኳን ቀጥሎ ቤተክርስቲን ስለሆነ ከክፍል ወጥተን እዛ ነበር ገብተን የምንቀመጠው። በሱ ምክንያት ሀይማኖት ላይ ጠንካራ እንድንሆን አድርጎናል።

አለም ሲኒማ፡- ግዕዝ ትማሩ ነበር?

ሀና፡- ግዕዝ አልነበረም ግን ፆም እንፆማለን። ግብረ ገብ እንማር ነበር። በአጋጣሚ እኔ ደግሞ አባቴ እዛው ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ቄስ ነው። ስለዚህ የተለየ ነገር ነበረው ደስ ይለኛል።

አለም ሲኒማ፡- ቤት ውስጥ ምን አይነት ልጅ ነበርሽ?

ሀና፡- እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። ብዙ ረባሽ አልነበርኩም ግን ጨዋም ልጅ አልነበርኩም(ሳቅ)

አለም ሲኒማ፡- ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገባብሽ ለየት ይላል አይደል?

ሀና፡- አዎ መጀመሪያ እርግጠኛ ነበርኩ ቴአትር እንደምማር ግን ሳይደርሰኝ ቀረና ደብረብርሃን የኒቨርሲቲ ተመደብኩ። ቤተሰቦቼ በጣም ተጨንቀው ነበር። እንዲያውም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታ መርሃ ግብር ቴአትር ያስተምራል ሲባል ቤተሰቦቼ ጋር ሁሉንም ወጭ ችለው እንዲያስተምሩኝ ጠይቄአቸው አቅሙ ባይኖራውም ለፍላጎቴ ሲሉ ብቻ ተስማተው ነበር። በኋላ ግን እኔን ሰው መክሮኝ ነው የተውኩት። እናትሽን የዚህን ያህል እወዳለሁ ካልሽ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ለምን ታስከፍያቸዋለሽ ሲለኝ ነው በጓደኛ ምክር ነገሩን ትቼ ወደ ደብረ ብርሃን የተጓዝኩት። በኋላ ግን አባቴ ሲያጣራ ተፈትኖ መግባት እንደሚቻል ነገሩኝ። አዲስ አበባ መጥቼ ስፈተን አለፍኩ። ያው በጣም ቤተሰቡ ተደሰተ እዚህ ቀጠልኩ ማለት ነው።

አለም ሲኒማ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምን አገኘሽበት?

ሀና፡- የመጀመሪያ ፊልሜን አንደኛ አመት ተማሪ እያለሁ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመጡ ዳይሬክተሮች ካስት አድርገውኝ ነው የመስራት እድሉን ያገኘሁት። ያ ብቻ ሳይሆን ከተፈጣሪ ፊልም በፊት የነበሩትን ፊልሞችና ስራዎች በሙሉ የሰራሁት ጊቢ ተማሪ ሆኜ ነው።

አለም ሲኒማ፡- ታዲያ ስራውን ከትምህርቱ ጋር ማስማማት አልከበደሽም ነበር?

ሀና፡- አዎ እኔ እንዲያውም ከትምህርቱ ይልቅ ስራው ላይ ትኩረት አደርግ ነበር እና ብዙ ችግሮች ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ስራውን ከትምህርቱ ስታስቀድም ሲያዩ ስለሚያናድዳቸው ከአስተማሪዎች ጋር መቀያየም ነበረ። ለኔ ግን ስኬታማ ጊዜ ነበረ። ምክንያቱም ጊቢ ሆኘ ባልሰራ ኖሮ የፈለገ ውጤት ቢኖረኝ ተመርቀህ በሲቪ ትወና ልትሰራ አትችልም።

አለም ሲኒማ፡- የሰራሻቸውን ፊልሞች ሁሉንም ታስታውሻቸዋለሽ?

ሀና፡- እረሳለሁ ግን ልሞክር። ድርሳነቤል፣ ለፍቅሬ ስል፣ ሰባት ሃያ አራት (ያልወጣ)፣ የሴት ፍቅር፣ ተፈጣሪ፣ አሁን ደሞ አስር። የዘለልኳቸው አሉ የጠፉብኝ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ብቻ ወደ ሰባት ፊልሞችን በመሪ ገፀ ባህሪነት ሰርቻለሁ። ከትልልቅ አርቲስቶች ጋር በደንብ የሰራሁት ተፈጣሪ ላይ ነው። ሁለተኛ ደግሞ በዳይሬክቲንግ እና በፕሮዲዩሰርነትም ተሳትፌበታለሁ።

አለም ሲኒማ፡- ድርሰት የሰራሽው አለ?

ሀና፡- አዎ ድርሰት እየሰራሁ ነው። ከዚህ በኋላ የሚወጡ ናቸው የኔ ድርሰቶች። በቅርቡ ራሴ ፅፌ ያዘጋጄሁት ፊልም ይወጣል። በትናንት የሚል ጊዚያዊ ርዕስ ያለው ፊልም ነው።

አለም ሲኒማ፡- ሌላው ዘመን ድራማ ላይ ትጫወቻለሽ እና ምን ያህል ጠቅሞሻል?

ሀና፡- ዘመን ላይ መሪ ተዋናይ ባይባልም በመሳተፌ ብዙ ነገሮችን አግንቼበታለሁ። ብዙ ሰዎችን አግኝቼበታለሁ። ልምዱም አለ።። ከካሜራ ጀርባ ጎበዝ ልጆች ያየሁበት ነው።

አለም ሲኒማ፡- የተማርሽው ቴአትር ነው ግን ቴአትር አልሰራሽም። ስለሚከብድ ነው ወይስ ምንድነው?

ሀና፡- አይደለም የኔ ፍላጎት ከመጀመሪያውም ፊልም ነው። ነገር ግን አገራችን ላይ የቴአትር እንጂ የፊልም ትምህርት አይሰጥም። ስለዚህ ለፊልም የሚቀርበውን ትማራለህ። ቴአትር ከፊልም የበለጠ ከባድ ነው በሚለው አልስማማም። ፊልምም የራሱ ከባድ እና አድካሚ ስራ አለው። የቴአትር ተማሪ ስትሆን ጥቅሙ የመፃፍ ችሎታ ታዳብራለህ።

አለም ሲኒማ፡- ከእጮኛሽ ጋር ተፈጣሪ ፊልም ላይ አብራችሁ ሰርታችኋል። ፊልሙ ላይ ነው ትውውቃችሁ?

ሀና፡- አይደለም። ቀደም ሲል ጅጅጋ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሆነን ነው ጓደኝነታን የሚጀምረው። ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ ነው ትውውቃችን። አለም ሲኒማ፡- ቀለበት አድርጋችኋል? ሰርጉን መቼ እንጠብቅ? ሀና፡- ወደዛው ሂደት ላይ ነን(ሳቅ)። ከዛ በፊት ቀድመን የምናስተካላቸው ነገሮች ላይ እየሰራን ነው። እግዚአብሔር ከፈቀደ በሚቀጥለው አመት ሁሉንም ነገር እንጨርሳለን።

አለም ሲኒማ፡- ስለ አስር ፊልም እናውራ እስቲ አስር ምንድነው?

ሀና፡- አስር ከቁጥርነት ባለፈ በዚህ ፊልም የራሱ ትርጉም አለው። ሰዎች በስህተትና በፍርደ ገምድልነት የምፈንጥረውን ማህበረሰብ አናውቀውም። የተጫወትኳት ገፀ ባህሪ የምታየውን ሁሉ ምናገባኝ ብላ የማታልፍ በራሷ ልክ የምታይ ናት። በመጥፎ አጋጣሚ ውስጥ ሳይቀር ተገኝታ የታገቱ ሴቶችና ህፃናትን ነፃ ለማውጣት ቤተሰቧን ከባድ ችግር ውስጥ የጣለች አሳዛኝ ሰው ናት። ደራሲና ዳይሬክተሩ ሰይፈሚካኤል ይባላል። ፕሮዲዩሰሩም ራሱ ነው።

አለም ሲኒማ፡- ፊልሙ ምን የተለየ ነገር አለው?

ሀና፡- መነሻ ታሪኩ በጣም ይገርመኛል። በተረፈ ዳይሬክተሩ የሰጠን ነፃነት ደስ ይል ነበር ሁሉም ያለ አለቃ ነው የሰራው።

አለም ሲኒማ፡- ስለሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ማለት የምትፈልጊው ነገር ካለ?

ሀና፡- ለሙያተኛው አቅም ማጎልበቻ ኮርሶች ቢሰጡ አሪፍ ነው። ፊልም ት/ቤት የለውም። ሌላ ግን ራሳችን ህብረት ቢኖረን እላለሁ። መንግስትም ማድረግ ያለበትን ቢያደርግ።

አለም ሲኒማ፡- ስለ ሲኒማ ቤቶች ምን አስተያየት አለሽ እኛን ጨምሮ?

ሀና፡- በሁለት መንገድ ነው የማየው። አንደኛ ለፕሮዲዩሰር በወቅቱ ሂሳብ መክፈል ቢቻል። በርግጥ ይህ እናንተን (ዓለም ሲኒማን) አይመለከትም። ዓለም ሲኒማ ወሩን ጠብቆ ደውሎ አስታውሶ ክፍያ ይሰጣል። ሌላው ግን ለምነህም ላታገኝ ትችላለህ። አሁን ድረስ ያልተቀበልነው የተፈጣሪ ፊልም ክፍያ አለ። ሁለተኛው ደግሞ የፕሮዲዩሰሮችን ድርሻ ትንሽ ማሳደግ ቢቻል። ምክንያቱም ከሲኒማ ቤት ጋር እኩል ተካፍሎ፤ 15 ፐርሰንት ግብር ከፍሎ፤ ለተዋንያን ለምናምን ከፍሎ ምን ይተርፈዋል ነው። በዚህ ከቀጠለ ፊልም ላይኖር ይችላል።

አለም ሲኒማ፡- ተፈጣሪ ሁለት እንደምትሰሩ ሰምተን ነበር የት ደረሰ?

ሀና፡- አዎ እስክሪፕቱ አልቋል። ነገር ግን ከቁጥር አንዱ በተሻለ ለመምጣት ጊዜ ወስደን እየሰራን ነው። ከዚያ በፊት ግን ሌሎች ፊልሞችን እንሰራለን።

አለም ሲኒማ፡- የቀረ ነገር አለ?

ሀና:- የለም። ምስጋና ነው ያለኝ። በመጀመሪያ በመንገዴ ሁሉ የረዳኝን ፈጣሪን አመሰግናለሁ። ቀጥሎ ግን ሁሌም ከፀሎቱ የማይለየኝን አባቴን በጣም አመሰግናለሁ። በመቀጠል ከእደሜዋ እና ከደስታዋ ላይ ቀንሳ ለኖረችልኝ እናቴን አመሰግናለሁ። እህት ወንድሞቼን ጓደኞቼን በሙሉ አመሰግናለሁ። እናንተም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።

አለም ሲኒማ፡- እኛም በሲኒማ ቤታችን እና በተመልካቾች ስም እናመሰግናለን።

in እንግዳችን